ቢሮው በፍርድ ቤቶች በተደረጉ ክርክሮች ከ4 ነጥ...

image description
- ውስጥ Laws    0

ቢሮው በፍርድ ቤቶች በተደረጉ ክርክሮች ከ4 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን ቻለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ባለፉት 11 ወራት በፍርድ ቤቶች በተደረጉ ክርክሮች ከ4 ቢሊየን 166 ሚሊየን ብር በላይ የህዝብና መንግስት ጥቅም ማዳን ቻለ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በበጀት ዓመቱ ባለፉት 11 ወራት በተደረገው የፍትሐብሔር ክርክር የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

በዚህም የፍትሐብሔር ጉዳዮች ክርክር በፍርድ ቤቶች የመርታት አቅም ከ96 በመቶ በላይ ለማድረስ ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት በፍርድ ቤቶች የመርታት አቅምን 92 ነጥብ 7 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

በፍርድ ቤቶች ውሳኔ ከተሰጣቸው 3 ሺህ 616 የፍትሐብሔር ክስ መዝገቦች ውስጥ 3 ሺህ 351 መዝገቦችን ለከተማ አስተዳደሩ ማስወሰን እንደተቻለም ጠቁመዋል።

በተሰጠው ውሳኔ መሰረት 4 ቢሊየን 166 ሚሊየን 369 ሺህ 267 ብር የሚገመት የአስተዳደሩን መብትና ጥቅም በፍርድ ቤቶች ማስከበር መቻሉን አስረድተዋል።

 

በተጨማሪም በአይነት 259 ቤቶች፣ 58 ሼዶች እንዲሁም 234 ነጥብ 59 ሄክታር መሬት የህዝብና መንግስት ጥቅም ማዳን ተችሏል ነው ያሉት፡፡

 

በተቃራኒው በተደረጉ ክርክሮች 265 መዝገቦች በመንግሥት ላይ መወሰኑን የገለጹት አቶ ተክሌ÷ ከዚህ ውስጥ 87 ውሳኔዎች ላይ ክርክር ቢደረግባቸው ተጨማሪ ወጪና ኪሳራ የሚያደርሱ በመሆናቸው በፓናል ውይይት መዘጋታቸውን ገልጸዋል።

 

178 መዝገቦች ላይ ደግሞ ይግባኝ በየደረጃው ተጠይቆባቸዋል ብለዋል።

 

በአድማሱ አራጋው


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.