ትውልድን በስነ-ምግባር፤ ተቋምን በአሰራር!̎
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ በአለም-አቀፍ ደረጃ ለ22ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ21ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን የፀረ-ሙስና ቀን ምክንያት በማድረግ “̎ትውልድን በስነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር!̎ በሚል መሪ ቃል የፍትሕ ቢሮ የበላይ አመራሮች እና ሰራተኞች በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ የፓናል ውይይት በማድረግ ተከበረ፡፡
የፍትሕ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ በአለም-አቀፍ ደረጃ ለ22ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ21ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው የፀረ-ሙስና ቀን እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድን መፍጠርና በአሰራር የሚመራ ተቋም መገንባት ያስፈልጋል በማለት ስነ-ምግባር ያለው ሀገር ተረካቢ ትውልድ መፍጠር ከሙስና የጸዳ የአሰራር ስርዓት ያለው ተቋም መገንባት ያስፈልጋል ሲሉ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡ኃላፊው አክለውም ተቋም አሰራር ሊኖረው እንደሚገባ በመግለጽ እንደ ፍትሕ ተቋም ህግ በማውጣትም ሆነ በማስፈጸም በከተማው አስተዳደር ሰፊ ድርሻ ያለው በመሆኑ ሙስናን ለመግታት ባለቤትም አባልም ስለሆንን ከፍተኛና ተደራራቢ ሚና አለብን በማለት የዕለቱን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ በፍቃዱ ባቀረቡት የውይት መነሻ ሰነድ መሰረት ሙስና ዜጎችን ለስቃይ፣ ለእንግልት እና ለከፋ ድህነት የሚዳርግ፣ አደገኛ የህዝብ ጠላትና ወንጀል እንደሆነ ገልጸው የሀገርን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በማናጋት ሀገርን እስከመበተን የሚያደርስ ድንበር ዘለል ወንጀል ነው ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም ሀገራዊ የፀረ-ሙስና ትግሉ በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ የትውልድ የስነ-ምግባር ግንባታና የግብረ-ገብነት ስራዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን አጠናክሮ መስራት ያስፈልጋል ብለው ሰላም የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት ከብልሹ አሰራርና ሙስና የፀዳ ትውልድ መፍጠርና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት አለብን በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በበአሉ አከባበርም የቢሮው አመራሮችና ሰራተኞች ስለ ሙስና ጽንሰ-ሃሳብ፣ ስለ ሙስና ባህርያት፣ ሙስናን በመከላከል የተወሰዱ እርምጃዎች እንዲሁም ሙስናን ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ሚና በሚሉ ይዘቶች ላይ የፓናል ውይይት አድርገዋል፡፡በመጨረሻም የጥያቄና መልስ ውድድር በማካሄድ የፓናል ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
ህዳር 22/2018
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.