የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት በ2018 በጀት ዓመት የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም ተገመገመ
የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት በ2018 በጀት ዓመት የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም ተገመገመ ።
ፍትሕ ቢሮ ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በሰው መነገድና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎች ተከላካይ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም የሰራቸውን ስራዎች ከፍትህ ቢሮ የተለያዩ የሥራ ክፍል የተወከሉ፣ ከትብብር ጥምረት አባላት ፣ ክ/ከተሞች እና የሚመለከታቸው አጋር ድርጅቶች በተገኙበት ግምገማውን አካሂዷል። በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ከሆፕ ፎር ጀስቲስ ካንትሪ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሶስና ይርጋ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልና የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን መከላከል ከሁሉም ዜጋ እንደሚጠበቅ እና ችግሩን ለመቅረፍ በጊዜ የለኝም መንፈስ በጋራ መሰራት እንዳለበት አንስተዋል ። በአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ሥር ያለው ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት በኩል የሚሰሩ በርካታ ባለድርሻዎችን አቀናጅቶ በጋራ ከመሥራት ጀምሮ በተደራጀ ሁኔታ የተሻለ የህግ አደረጃጀትን በመፍጠር ከሌሎች አቻ ክልሎች ጋር ጭምር የተጀመሩ የቅንጅት ሥራዎች ለሌሎችም እንደ መልካም ተሞክሮ ልሆን የሚችል መሆኑን ገልጸዋል ። በፍትህ ቢሮ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ብርሃኑ በበኩላቸው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ከመከላከል ጀምሮ የሚሰሩ በርካታ ሥራዎችን መሥራት የመንግስት ግዴታ ብቻ ሳይሆን የብዙ ባለድርሻ አካላትም ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን አስታውሰው ይህን የዜግነት እና ሀገራዊ ሃላፊነት ከመንግስት ጋር ተደምረው እየሰሩ የሚገኙ እንደ ሆፕ ፎር ጀስቲስ ያሉ መ.ያ. ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል ። ኃላፊው የ11ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት በ5 ዋና ዋና ስትራቴጂክ ግቦች መነሻ ያደረጉ ሲሆን እነዚህም የግንዛቤ ሥራዎች በአደባባይ በሚዲያ በመድረክ የተሰጠ መሆኑን ፣ ወንጀል መከላከልና ህግ ማስከበር ሥራዎች ፣ የፍልሰት ጉዳዮች ምክር ቤትና የትብብር ጥምረት አደረጃጀት ከማጠናከር አንፃር የተሰሩ ሥራዎች ፣ የወንጀል ጥቆማ በነፃ ስልክ ጥሪ 6073 መቀበልና መረጃ የመስጠት እንዲሁም የወንጀል ተጋላጭነት ቦታ ልየታ ጥናት ሥራዎች በአጠቃላይ በትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ፣ በሥራ ቡድኖች እና በሁሉም ክ/ከተሞች የተሠሩ እንዲሁም የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠና ጨምሮ የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት በርካታ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸው አቅርበዋል። በትብብር ጥምረት ሥር ካሉ የሥራ ቡድኖች አንዱ በሆነው የሥራና ክህሎት ቢሮ በኩል በግንዛቤ ፈጠራ ፣ የውጪ አገር የሥራ ስምሪትና ተጎጂዎችን ድጋፍና መልሶ ከማቋቋም ጋር በተያያዘ በ11 ወራት ውስጥ የተሰሩ ዝርዝር ተግባራት ሪፖርት በሥራና ክህሎት ቢሮ የውጪ አገር ሥራ ስምሪት ቡድን መሪ በሆኑት በአቶ ሳሙኤል ግርማ ቀርቧል ። በመጨረሻም በቀረቡት በሁለቱም ሪፖርቶች ላይ ከማዕከል ፣ ከክ/ከተሞች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከተውጣጡ ተሳታፊዎች ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን ጥንካሬዎችን የማስቀጠል እና በክፍተት በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ተጨማሪ ስራዎች መስራት እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.