ለህገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር ወንጀል ተጋላጭ የሆኑ ህፃናትና ሴቶች መብት ጥበቃ እና የተቀናጀ የትብብር አሰራር ማጠናከርን በተመለከተ የውይይት መድረክ ተካሄዷል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከ justice For All-PF Ethiopia ጋር በመተባበር ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች የህግ ጥበቃ በማሻሻል ዙርያ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ አካሄዷል ።በመድረኩ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል።የአ.አ ፍትህ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አሰፋ መብራቴ በንግግራቸውም የወጡ ህጎች ተፈጻሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ በመጠቆም በአካባቢው ለሚገኙ ተጋላጭ ወገኖች፣ ሴቶች፣ ህፃናት እና መደበኛ ባልሆነ ስራ ላይ ለተሰማሩ ዜጎች ፈጣንና ተደራሽ የሆነ የህግ ድጋፍ፣ የምክር አገልግሎት እና የፍትህ አሰጣጥ ስርአት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ፍትህ ቢሮም ከተለያዩ ተቋሞችና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ከሴቶችና ሕጻናት መብት ጥበቃ ከማጠናከር አንጻር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።የፍትህ ቢሮ አማካሪ ወ/ሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴ እንዳሉት justice For All-PF Ethiopia የቢሮው ተባባሪ በመሆኑ ምስጋናቸውን በማቅረብ በህጻናት ላይ በሚደርሱ የተለያዩ ችግሮችን ለማቃለል እና በዘላቂነት ለመፍታት ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ያስፈልጋል ብለዋል። በፍትሕ ቢሮ በሰው የመነገድና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ተከላካይ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ብርሃኑ በበኩላቸው የዜጎች ተጋላጭነትን በመጠቀም የሚፈፀም በሰው የመነገድ ድርጊት የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል በመሆኑ ሕገወጥ ፍልሰትን ለመከላከል የወጡ የሕግ ማዕቀፎችን እና ወንጀሉን ለመከላከል ከማዕከል እስከ ወረዳ ያለውን አደረጃጀት፣ የትብብር ማዕቀፍ መነሻ ያደረገ ሰነድ አቅርበዋል።በከተማዋ ተጋላጭነት ባላቸው አከባቢዎች የተቀናጀ ምላሽ አሰጣጥ ለማረጋገጥ የሚያስችል የትብብር ማዕቀፍ ሰነዱን ያቀረቡት በኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ረቂቅ ዳይሬክተር በሆኑት አቶ አዲስ ጌትነት እና በህጻናት መብት ጥበቃ ከማሻሻል አኳያ በቀረቡ ሰነዶች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል ።በመጨረሻም በተነሱት ሃሳብ አስተያየት ከፍትህ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አሰፋ መብራቴ ፣ ከሴቶችና ሕጻናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወ/ሮ ጸሀይ ኪባሞ፣ ከjustice For All-PF Ethiopia ዋና ፕሮግራም ሃላፊ ዶ/ር ጌታሁን አለማየሁ እንዲሁም በጠበቃ ጌድዮን ሲሳይ አወያይነት መድረኩ ተጠናቋል።
ጥቅምት 7/2019
ፍትህ ቢሮ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.